በክልሉ የገጠር የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የገጠር የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህርዳር፤ ጥር 21/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የገጠር ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ ተቋማት የ2018 በጀት ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በባህርዳር እየተካሄደ ይገኛል።
የዘርፉ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ በቡና ልማት እየታየ ያለው ውጤታማነት ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን አቅም መፍጠሩንም ነው ያነሱት።
ባለፉት ስድስት ወራት ትራክተሮችን ጨምሮ በርካታ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት የመስኖ ልማት መካሄዱን አመልክተዋል።
የገጠር ሽግግርን ለማፋጠን እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨባጭ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው ያሉ አመራሮች ይህን ስኬት ለማላቅ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።