ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዩን እንግልት ቀንሷል

ደሴ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የተገልጋዩን እንግልት መቀነሱን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።


 

በከተማዋ በአንዳንድ ተቋማት ላይ በግልጽ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ይህን ክፍተት ለመሙላትና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ገልጸዋል።

በማዕከሉ የተለያዩ ተቋማት በተቀናጀ መልኩ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው መሰረተ ልማት መሟላቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህም ተገልጋዩ በአጭር ጊዜ የሚፈልገውን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሎታል ነው ያሉት።


 

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን በዛብህ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ 14 የከተማ አሥተዳደሩና የፌዴራል ተቋማት 79 አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በማዕከሉ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል የመሬት ነክ ጉዳዮች፣ የገቢዎችና ንግድ፣ የቴሌኮም፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የባንክ የዲጂታል መታወቂያና ሌሎችም ይገኛሉ ብለዋል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ቦታዎች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በመሰብሰብ የተጠቃሚውን ጊዜና ጉልበት መቀነስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ከማዕከሉ ተገልጋዮች መካከል አብዱ ሰይድ በማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ማግኘት መቻላቸው ጊዜና ወጪን መቆጠቡንና ብልሹ አሠራርን ከማስቀረት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በአጽንኦት ገልጸዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም