ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ለሌሎች ሀገራት ዓርዓያ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ለአፍሪካ ሀገራት ዓርዓያ ይሆናል ሲሉ በአፍሪካ ሕብረት እና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተጠሪ ስቴፈን ካግቦ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ሀገሪቷ በፈጣን እድገት ላይ መሆኗን ማሳያ ናቸው ሲሉም ለኢዜአ ገልጸዋል።

የኃይል አማራጭ ዐቅሟን ለማጠናከር ያከናወነቻቸው ተግባራት ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የጎላ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።

ኢትየጵያ በልማት ዓርዓያነት ረገድ ለሌሎች ሀገራት የምታካፍለው ሰፊ ተሞክሮ እንዳላትም ጠቅሰዋል።

በተለይም የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ የምታደርገው ትኩረት ከኢንዱስትሪ ባሻገር ለሌሎች ማኅበራዊ ዘርፎችም ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያላት ቅንጅታዊ አሠራር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለሌሎች ሀገራት እንደ ሞዴል ሊወሰድ እንደሚችል ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ከአጋር አካላት ጋር የሚያከናውነው ቅንጅታዊ አሠራር በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና መሰል ሥራዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የዩኒዶ ትስስሮችን ማመቻቸትና የቴክኖሎጂ ልውውጥን ከማበረታታት አኳያ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ መጪ ጊዜ ብሩህ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም