ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን- ሲቪክ ማኅበራት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን- ሲቪክ ማኅበራት
ጅግጅጋ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ገለጹ።
የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሐመድ አሕመድ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር ከመፍታት ባለፈ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ አስፈላጊ ግብዓት የሚገኝበት ነው።
ወጣቱም ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ በማጠናከር የተሻሉ ሥራዎችን ለማከናወን መዘጋጀቱን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ወጣቱ አለመግባባቶችን በሠለጠነ መልኩ የመፍታት ባህልን እንዲያጎለብት ከማድረግ አንፃርም የላቀ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር ኒኢም አብዱላሂ ናቸው።
ኮሚሽኑ ምክክሮች እንዲደረጉ እያከናወናቸው ያሉ ቀሪ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ከዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ምክክሩ የታለመውን ውጤት እንዲያመጣ እንደ ሲቪክ ማኅበራት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው ለኢዜአ ያረጋገጡት።