ቀጥታ፡

ሲቪክ ማኅበራት ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

ሰቆጣ፤ ጥር 21/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚከናወኑ ተግባራት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ ሲቪክ ማኅበራት ገለፁ።


 

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመምህራን ማኅበር ሊቀ መንበር ከፍያለው አስፋው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ በሚከናወኑ ተግባራት የማኅበሩ አባላት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ተዘጋጅተናል።



 
አካል ጉዳተኞች በጠቅላላ ምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ በአሥተዳደሩ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አባል እሸቱ ደምሴ ናቸው።

አካል ጉዳተኞች የመራጭነት ካርድ ቀድመው እንዲይዙ እንዲሁም በታዛቢነት እንዲሳተፉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል።


 

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሀገር ሽማግሌዎች ማኅበር ሰብሳቢ አብርሃ ገብረ መድኅን በበኩላቸው፤ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ማኅበራቸው በትጋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

አረጋውያን የመራጭነት ምዝገባውን በወቅቱ እንዲያከናውኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ምርጫው አካታችና ፍትሐዊ እንዲሆን ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ ያረጋገጡት ደግሞ በአማራ ወጣቶች ማኅበር የዋግኽምራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አስተባባሪ ወንድሙ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው።

ወጣቱ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ በመያዝ ሀገራዊ ኃላፊነቱ እንዲወጣ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም