ቀጥታ፡

የኢኮኖሚና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት በትብብር እንሰራለን

አዲስ አበባ፤ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-የኢኮኖሚና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት በትብብር እንደሚሰሩ የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ ገለጹ።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ከአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ቲ ላንዳው ጋር በትብብር መስራት በሚቻልባቸው የሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፤ አፍሪካ በብዙ ፀጋዎችና ሀብቶች የተሞላች አህጉር ናት ብለዋል።

የአፍሪካን ሃብቶች ለዜጎቿ ተጠቃሚነት ለማዋልም በሚከናወኑ ተግባራት አህጉሪቷ የአሜሪካንን የዕውቀት፣ የሙያ፣ የአቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ትብብር ትፈልጋለች ብለዋል፡፡


 

የህብረቱ አባል ሀገራት የውስጥ አቅማቸውን በማሳደግ፣ በሲቪል እና ንግድ ማህበረሰብ አማካኝነት የልማት መርሃ ግብሮችን በራሳቸው ገንዘብ በመደገፍ ተስፋ ሰጪ አቅም እየገነቡ መሆኑን አንስተዋል።

የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲና ትብብር ስርዓት ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ሀገራትና በአሜሪካ መካከል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ ዕድገትን ማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ቲ ላንዳው በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን ሰላምንና የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ከአባል ሀገራት ጋር በመተባበር ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ብለዋል።

​የአፍሪካ ህብረትና አሜሪካ በጋራ ደኅንነት፣ ሰላምና እና ብልጽግና ጉዳዮች በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የበለፀገች አፍሪካ መኖር ለአሜሪካም ጥቅም ነው ያሉት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፤ አፍሪካ ያላትን ዕምቅ የኢኮኖሚና የንግድ ዕድሎችን በጋራ ጥቅም ላይ ለማዋል እንሰራለን ብለዋል፡፡

አሜሪካ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መርህ እንዳላት በማንሳት፤ የኢኮኖሚ ዕድገት ዕድሎችን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ከአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል አንደርሰን ጋር ያደረጉት የሥራ ጉብኝትም አሜሪካ የአሕጉሪቷን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ካላት ቁርጠኝነት የሚመነጭ መሆኑን አስረድተዋል።

አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ በማንሳት፤በአፍሪካውያን የውስጥ ጉዳይ ማንም ጣልቃ መግባት እንደሌለበት እናምናለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም