ቀጥታ፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ኢንቨስትመንት የማስፋት ፍላጎት አላት-የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው

አዲስ አበባ፤ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፦አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ተደራሽነት ለማስፋት እና ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት የሀገሪቷ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ገለጹ።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና የኢትዮጵያና አሜሪካን ትብብር እንዲሁም እያደገ የመጣውን አጠቃላይ አጋርነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው።


 

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ጠንካራ ለውጥ እንደታየባቸው ገልጸው፥ የኢኮኖሚ እድገት አዝማሚያ እና በቁልፍ ዘርፎች ያለው የኢንቨስትመንት ምህዳር የተሻለ መሻሻል እንዳሳየ የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ጠንካራ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸው፥ በቅርቡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ጤና ዘርፍ ያደረገችውን ድጋፍ ጠቅሰዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

በሌላ በኩል ሚኒስትሩ ለአሜሪካው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ ግንባታው ስለተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ገለጻ አድርገዋል።

አየር ማረፊያው ለእድገት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና ንግድ መሳለጥ ያለውን ስትራቴጂካዊ ሚና ያነሱ ሲሆን የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት እና ተቋራጮች ፕሮጀክቱን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።


 

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው፥ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች በማድነቅ አሜሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ እና አሜሪካን አጋርነት ለማጠናከር፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን ለመደገፍ የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም