ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በኢነርጂ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በኢነርጂ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት በኢነርጂ መስክ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትስስር ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በ27ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ገብተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ከስብስባው አስቀድሞ ከአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሜሪያም ፌራን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በስብስባው ላይ ሚኒስትሩ እና ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሏ የሁለቱን ወገኖች ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪዶር በሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ አስመልክቶ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአውሮፓ ህብረት ለማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
በተለይም ህብረቱ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ መስመሮችን በታዳሽ ኃይል እና በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በማዘመን ዘላቂ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ የኃይል አቅርቦት የማረጋገጥን አላማ ላለው ፕሮግራም (RISED) የሚያደርገውን ድጋፍ ለአብነት አንስተዋል።
27ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብስባ ለኃይል ማሰራጫ መሰረተ ልማቶች እና ለቀጣናዊ የኢነርጂ ትስስር ስራዎች የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኢነርጂ አቅርቦትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።