ቀጥታ፡

የዴሞክራሲ ተቋማት ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለመልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው

ባህር ዳር፣ጥር 20/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የዴሞክራሲ ተቋማት ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለመልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በክልሉ የሚገኙ የዴሞክራሲ ተቋማት ስራ ክንውን የግብረመልስ ሪፖርት ላይ ከአማራ ክልል ምክር ቤት አመራሮችና ከተቋማቱ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ በክልሉ የዴሞክራሲና የሚዲያ ተቋማት የስራ እንቅስቃሴ በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማቱ በተለይም ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለመልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብትና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማትም ለሰብአዊ መብት መከበርና አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ድርሻቸውን  እየተወጡ መሆናቸውን ተገንዝበናል ሲሉ ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ጋሻው ዳኘው፤ በክልሉ የሚገኙ የፌደራል የሚዲያና የዴሞክራሲ ተቋማት ተልዕኳቸውን በመፈጸም ረገድ ውጤታማ ስለመሆናቸው አንስተዋል።

በሰላም እና የጋራ ትርክት ግንባታ፣ ሀገራዊ የምክክር ሂደት፣ የልማት ስራዎችን የማስተዋወቅና ሌሎች ተግባራት ላይ የሚዲያዎቹ ጥረት መልካም መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፤ የዴሞክራሲ ተቋማት የክልሉን ህዝብ በማገልገል ረገድ አበረታች ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን አይተናል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የሚዲያና የዴሞክራሲ ተቋማቱ መልካም ጅምሮች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም