በቀን እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ ማቅረብ የሚያስችለው የጭቋላ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ ነው-የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በቀን እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ ማቅረብ የሚያስችለው የጭቋላ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ ነው-የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-በቀን እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ ማቅረብ የሚያስችለው የጭቋላ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ገለጸ።
በሌላ መልኩም የገርቢ ንጹህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቀን እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ የማቅረብ አቅም ያለው የጭቋላ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
22 የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የሲቪልና የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትም በተሳለጠ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጭቋላ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት በከፊል እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፥ በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ ሙሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም የምዕራብ አዲስ አበባ፣ ጀሞ፣ ቤቴል፣ ሳር ቤት እንዲሁም የአቃቂ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ ለመዲናዋ ተጨማሪ ውኃ የማቅረብ አቅምን የሚያሳድገው የገርቢ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታን ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በቀን ከ73 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፤ በርካታ የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ በመዲናዋ ያለውን የውኃ አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር አስታውቀዋል።
የውኃ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ወደ ሥራ ለማስገባት ተጠንተው የተቀመጡ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የግንባታ ሥራቸውን ለማስጀመርም የፋይናንስ ማፈላለግ ሥራዎች ጎን ለጎን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።