ቀጥታ፡

ዜጎች በመልዕክት መላላኪያ አማራጮች በሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፦ ዜጎች በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ አማራጮች ለሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች እና የማጭበርበር ድርጊቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳሰበ።

ማህበረሰቡ የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)፤በኢትዮጵያ የዲጂታል ትስስር መስፋፋትን ተከትሎ በዋትሳፕ (WhatsApp)፣ በቴሌግራም (Telegram) እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ፕላትፎርሞች አማካኝነት በዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችና የማጭበርበር ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸዉን በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጥ መቻሉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ የሚካሄዱ የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን፣ ዓለም አቀፍ መድረኮችን እና የኦንላይን ስብሰባዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የሳይበር ወንጀለኞች የእነዚህን ኩነቶች ስም ለሀሰተኛ ድርጊቶቻቸው መጠቀሚያ እያደረጉት እንደሚገኙ አመልክቷል።

እነዚህ አካላት የማህበረሰቡን የግል መረጃ ለመስረቅ፣ የባንክ ሂሳቦችን ለመመዝበር እና የዲጂታል ደህንነትን ለማናጋት በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ መሆኑን አስተዳደሩ በክትትልና በምርመራ ማረጋገጡን ገልጿል።

የሳይበር ጥቃቶች የሚፈጸሙት ማህበረሰቡ ትኩረት የሚሰጣቸውን "ተፈላጊ" እና "ወቅታዊ" የሆኑ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በተዘረጋ ስልታዊ የማታለያ ዘዴ መሆኑን ተጠቁሟል።

አጭበርባሪዎቹ "ለሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች የተዘጋጀ ነጻ የኢንተርኔት ፓኬጅ"፣ "ልዩ የስራ ቅጥር" ወይም "ይህ የስብሰባ መሳተፊያ ሊንክ ነው፤ ከፍተው ይግቡ" የሚሉ አሳሳችና ማራኪ መልዕክቶችን በማሰራጨት ተጠቃሚዎች በመልዕክቱ ውስጥ የተካተተውን ሊንክ (Link) እንዲጫኑ እንደሚያደርጉ የገለጸው አስተዳደሩ፥ ይህ ድርጊት ተጠቃሚው ሳያውቀው ወደ አጥፊ ተልዕኮ ወዳላቸዉ ድረ-ገጾች እንዲያመራና ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርግ የመጀመሪያው የወንጀለኞች እርምጃ እንደሆነ አመልክቷል።

ጥቃት አድራሾቹ የአንዳንድ ግለሰቦች የግንዛቤ እጥረትና ትኩረት ማጣት የተነሳ የሚላኩላቸውን ሊንኮችና መልዕክቶች በጥንቃቄ የመመርመር ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ ወንጀለኞቹ ይህን ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ነው ያለው።

ይህ አይነቱ ጥቃት ከግለሰቦች መረጃ ስርቆት ባለፈ፣ በእጃቸው የሚገኙ ሚስጥራዊ መረጃዎች በጠላፊዎች እጅ እንዲወድቁ በማድረግ በሀገር ደህንነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑን አስተዳደሩ በጥብቅ አሳስቧል።

በዚህም ተጠቃሚዎች የተላከላቸውን ሊንክ ሲጫኑ ወይም የተጠየቁትን መረጃ ሲሞሉ፣ የዋትሳፕ ወይም የቴሌግራም አካውንታቸው ወዲያውኑ በጠላፊዎች ቁጥጥር ስር እንዲዉል እንደሚያደርግም ነው በመግለጫው ላይ የሰፈረው።

ወንጀለኞቹ አንዴ የአንድን ሰው አካውንት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የተጠለፈውን አካውንት በመጠቀም በተጎጂው ስም ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶቹና ለስራ ባልደረቦቹ "ድንገተኛ ችግር አጋጥሞኛል" የሚሉ የሀሰት የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን ይልካሉ።

ይህም ድርጊት በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መተማመን ከመሸርሸሩ ባለፈ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማጭበርበር እንዲመዘበር በማድረግ መጠነ-ሰፊ የኢኮኖሚና የስነ-ልቦና ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ነው ተቋሙ ያስታወቀው።

ከላይ የተጠቀሱና መሰል የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ፣ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኢመደአ አሳስቧል።

ከማይታወቁ ወይም ካልተረጋገጡ አድራሻዎች በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች መድረኮች የሚላኩ ሊንኮችን ካለመክፈት ባለፈ፣ አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሱ ወዲያውኑ "Report" እና "Block" በማድረግ የጥቃቱን ስርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

በተጨማሪም ማንኛውንም አይነት ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል ወይም በስልክ የሚላክ የማረጋገጫ ኮድ (Verification Code) ለማንም አካል አለመስጠት ለዲጂታል ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል።

አስተዳደሩ እያንዳንዱ ተጠቃሚ በተለይም ማህበረሰቡ በመተግበሪያዎቹ ላይ የሁለትዮሽ ማረጋገጫ (Two-Step Verification) በአስቸኳይ እንዲተገብር መክሯል።

ይህ የቴክኖሎጂ የመረጃ ጠላፊዎች የግለሰቦችን አካውንት በቀላሉ እንዳይቆጣጠሩ የሚያደርግ እና ተጨማሪ የደህንነት ቁልፍ የሚፈጥር አስተማማኝ የመከላከያ ዘዴ እንደሆነ ገልጾ ዜጎች ይህንን ቀላል ግን ውጤታማ የሆነ የደህንነት ጥንቃቄ ተግባራዊ በማድረግ፣ ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ከታገዙ የማጭበርበር ድርጊቶች ሊታደጉና የሳይበር ወንጀለኞችን ሴራ ሊያከሽፉ እንደሚገባ አስተዳደሩ ያሳሰበው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እነዚህን የሳይበር ወንጀለኞች በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የጸጥታና የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ማህበረሰቡ ማንኛውም የሳይበር ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥመው ወይም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በነጻ ስልክ መስመር 933 በመደወል ለኢመደአ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።

የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በንቃትና በጥንቃቄ በመምራት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በጋራ መጠበቅ እንደሚገባም መግለጫው አትቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም