በከተማዋ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ውጤታማ የሰላምና ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ውጤታማ የሰላምና ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል
ደሴ፤ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ በ2018 ግማሽ በጀት ዓመት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ውጤታማ የሰላምና ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ አስታወቀ።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፣ በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታና የልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት ተሰርቷል።
ሕብረተሰቡ በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ልማቱን ለማፋጠን በከፍተኛ ተነሳሽነት መሳተፉንም ነው ያመለከቱት።
በኮሪደር ልማት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በገበያ ማረጋጋትና በከተማ ግብርና ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን ጠቅሰው፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ ከ16 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አብራርተዋል።
በግማሽ ዓመቱ የተገኙ ውጤቶችን በማላቅ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አብዱልሃሚድ ይመር በበኩላቸው፣ በከተማዋ በሰፈነው ሰላም የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑና የሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ማስቻሉን ተናግረዋል።
የሆጤ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምንይሻው በሪሁን እና የቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ታምራት ጋሻው በከተማዋ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማቃለል መቻሉን ነው የገለጹት።
በግማሽ ዓመቱ በገቢ አሰባሰብ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በከተማ ልማትና ውበት እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን የበለጠ በማጠናከር የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።