ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት ያለው ነው 

ሚዛን አማን፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ  ህጋዊና ታሪካዊ መሰረት ያለው  መሆኑን  የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ  መምህራን ተናገሩ፡፡ 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ መምህራን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ፣ ህጋዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት አለው።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ አማረ ፋንታው (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪካዊና ህጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን የታሪክ ሰነዶችን በማጣቀስ ይናገራሉ።


 

ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት በማድረግ የተመዘገበውን ፈጣን እድገት ለማስቀጠልና ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን  ለማጉላት ጉዳዩ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

ይህም ለሀገርና ለቀጣናው በጋራ መልማት አጋዥ  በመሆኑ ለተግባራዊነቱ  የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ሀገራዊ የዕድገት ጉዞን ዘላቂ የማድረግ ተስፋ የተጣለበት ሰፊ አንድምታ ያለው መሆኑንም ነው ያነሱት።


 

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ  ካሳሁን ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላት ሰፊ የሕዝብ ቁጥር፣ የቆዳ ስፋትና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመመለስ  የባሕር በር ባለቤትነትን  ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ እያደገ የመጣውን የወጪና ገቢ ምርት በአግባቡ በማስተናገድ የንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ መሰረታዊ  ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት ያደረገ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም