የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ድጋፍና ክትትል ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ድጋፍና ክትትል ይጠናከራል
ጂንካ ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ የተመራ ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን በና-ፀማይ፣ ሐመር እና ኛንጋቶም ወረዳዎች በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
ቡድኑ የመስኖ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የአዳሪ እና መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ የእንስሳት ህክምናና የሽያጭ ማዕከላትን ጨምሮ ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ጎብኝቷል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ተግባራዊ የተደረጉት እነዚሁ የልማት ፕሮጀክቶች በነዋሪዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
መንግስት የክልሉ ህዝብ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ ያደረጋቸው የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑም ምክር ቤቱ ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያረጋገጡት።
የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው፥ ምክር ቤቱ የድጋፍና ክትትል ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉ ይበልጥ ስኬታማና የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ያግዛል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ካሉት ፕሮጀክቶች ባሻገር ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ 68 የሚደርሱ የመስኖና የውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ ያሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ፣ የመንገድና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የኦሞ ወንዝ ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ ለመጓጓዣነት እና ለዓሳ ማስገር ብቻ ይውል እንደነበር የገለጹት ደግሞ የካራ -ዱስ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ላሌ ሙኮ ናቸው።
አሁን መንግስት በአካባቢው የመስኖ አውታር በመገንባቱ ወንዙን ለተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋል መቻሉን አክለዋል።
በአካባቢው በተገነቡት የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶችም ነዋሪውን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።