በተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር ለምነት በመጨመሩ የአርሶአደሮች ምርታማነት አድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር ለምነት በመጨመሩ የአርሶአደሮች ምርታማነት አድጓል
ወላይታ ሶዶ ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡- በተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር ለምነት በመጨመሩ ምርታማነታቸው ማደጉን በወላይታ ዞን የኦፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
"እመርታ በተቀናጀ ተፋሰስ ለብልፅግናችን!" በሚል መሪ ሃሳብ የ2018 ዓ.ም ዞናዊ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዞኑ ኦፋ ወረዳ ቡሻ ቀበሌ ጋዬ ንዑስ ተፋሰስ ላይ ተካሄዷል።
በወቅቱም ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ በተፋሰስ ልማት ስራው የአፈር ለምነት በመጨመሩ ምርታማነታቸው አድጓል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አርሶ አደር በቀለ ቶጋ፤ ለበርካታ ዓመታት በተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልፀው በአካባቢው የልማት ስራው ከመከናወኑ በፊት በነበረው የአፈር በጎርፍ መሸርሸር ሳቢያ መሬቱ ተራቁቶ እንደነበር ገልጸዋል።
ሆኖም ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነት እንዲጨምርና ምንጮች እንዲፈልቁ በማድረጉ በስራው በዘላቂነት እንድንሳተፍ መነሳሳትን ፈጥሮልናል ብለዋል።
የአየር መዛባትና የአካባቢ መራቆት ከሁሉም በላይ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ የከፋ በመሆኑ አካል ጉዳተኝነት ሳይበግረኝ የሚጠበቅብኝን እየተወጣሁ እገኛለሁ ያሉት ደግሞ አርሶ አደር መሰለ መንገሻ ናቸው።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከዚህ ቀደም የተራቆቱ አካባቢዎች አገግመው ምርት እንዲሰጡ ከማድረጉም ባሻገር ለኑሮ ምቹ አካባቢን ፈጥሮልናል ብለዋል።
የአፈር ለምነት በጨመረባቸው እና ምንጭ በፈለቀባቸው አካባቢዎች የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የኦፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዲሱ ወርቁ በበኩላቸው፤የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለዘላቂ የግብርና ልማት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በወረዳው በዘንድሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ከ31 ሺህ በላይ ህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ20 ንዑስ ተፋሰሶች ከ2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።
በዞኑ ባህል ሆኖ የቀጠለው የተፋሰስ ልማት ስራ በስነ-አፈር እና በስነ-አካላዊ ስራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች በማገገማቸው ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዘማች ሶርሳ (ዶ/ር) ናቸው።
ይህንን ውጤት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ በዞን ደረጃ በ315 ተፋሰሶች ከ46 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የወላይታ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አማረ አቦታ (ዶ/ር)፤ በዞኑ የተፋሰስ ልማት ስራ ከተጀመረ ወዲህ የተራቆተ መሬት በማገገሙ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተገቢው ማስረጽ እንደሚገባ ገልጸው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በመሳተፍ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።