ቀጥታ፡

ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር የለማ የመኸር ሰብል እየተሰበሰበ ነው

ሮቤ ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ባሌ ዞን ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር የለማው የመኸር ሰብል በሜካናይዜሽን ታግዞ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ቡሳ ጎኖፋ የገዳ ስርዓት አካል ሲሆን፤ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥመው እርስ በእርስ ተደጋግፎ ችግሩን የሚያልፍበት ዘዴ ነው።


 

አሁን ላይ ሥርዓቱ ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው ከተደረገ በኋላ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው።

የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነው የቡሳ ጎኖፋ ሥርዓት ውጤታማ ከሆነባቸው የክልሉ አካባቢዎች የምሥራቅ ባሌ ዞን ተጠቃሽ ነው።


 

የምሥራቅ ባሌ የቡሳ ጎኖፋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ አብዱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቡሳ ጎኖፋ ስርዓትን ይበልጥ ለማጠናከርና ተቋማዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ባለፈው መኸር አዝመራ በ2 ሺህ 153 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ማልማት ተችሏል።

የለማው መሬት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ 700 ሄክታር  ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።


 

በመኸር አዝመራው ከለማው መሬትም ከ65 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸው እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ በሜካናይዜሽን በመታገዝ 38 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ቀሪው በመኸር አዝመራ የለማ ስንዴ ከብክነት በጸዳ መልኩ በሜካናይዜሽንና በሰው ኃይል ታግዞ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ አውስተዋል።

የቡሳ ጎኖፋ ስርዓትን ይበልጥ ለማጠናከር ከሰብል ልማቱ ጎን ለጎን የሥርዓቱን ዓላማ ብዙዎች ዘንድ በማስረጽ 370 ሺህ  አባላት ማፍራት መቻሉን አስረድተዋል።


 

ቡሳ ጎኖፋ በአሁኑ ወቅት ከ28 ሚሊዮን በላይ አባላት በክልሉ ያሉት ሲሆን ከአባላቱ የሚሰበሰበው ዓመታዊ መዋጮ 3 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ተመልክቷል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በምሥራቅ ባሌ ዞን በመገኘት የቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትና ሌሎች የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም