የኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦትና ጤናማ ምኅዳር ግንባታ ውጤቶች ለአሕጉራዊ አጀንዳ 2063 ግቦች ስኬት ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦትና ጤናማ ምኅዳር ግንባታ ውጤቶች ለአሕጉራዊ አጀንዳ 2063 ግቦች ስኬት ወሳኝ ድርሻ ይኖራቸዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ጤናማ ምኅዳር ግንባታ ውጤቶች ለአሕጉራዊ አጀንዳ 2063 ግቦች ስኬት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖራቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዘንድሮው 39ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ’’ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 7- 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የውሃ አቅርቦት ዘላቂነትና ንጽህና አጠባበቅ፣ ጤናማ ማህበረሰብና ጠንካራ ምኅዳር ግንባታ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና የዜጎች ኑሮ ማሻሻያ ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የንጹህ ውሃና የኃይል አቅርቦት የልማት ስኬቶች ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳዎች ጋር ተጣጥመው እየተተገበሩ ነው።
በንጹህ መጠጥ ውሃና ኃይል አቅርቦት እንዲሁም በዜጎች ጤናማ የመኖሪያ ምኅዳር ግንባታ መስክ በአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዘላቂ ልማት ግቦች ጋር ተሰናስለው የሚተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ በዘላቂ የልማት ግቦች መነሻነት ከ80 ሚሊየን በላይ ዜጎቿን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለች አስረድተዋል።
በ2030 ዓ.ም ዕቅድም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በቤታቸው ወይም በአቅራቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ስኬታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ በሆኑ የኢትዮጵያ አካባቢዎችም በመንግስትና በፕሮጀክት በጀት ድርቅን የሚቋቋም አስደናቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መሠረተ ልማት መገንባቱን አስታውቀዋል።
በኃይል አቅርቦት ዘርፍም የኃይል አማራጭ ልማትን በማስፋት በከተማና ገጠር ከሥነ-ምኅዳር ደኅንነት ጋር የተጣጣመ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተተገበረው የወንዝ ዳር ልማት የውሃ ሀብት ደኅንነትን በመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም በአዲስ አበባ እና በሁሉም የውሃ አካላት በወንዝ ዳር ልማት የውሃ ሀብት ብክለትን በማስቀረት ዜጎች ንጹህና ጤንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የሚኖሩበትን ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ በንጹህ መጠጥ ውሃና በኃይል አቅርቦት እንዲሁም በውሃ አካላት ደኅንነት ያስመዘገበችው ውጤት ዘላቂ የልማት ግቦች በማሳካት አህጉራዊ ተምሳሌትነቷን እያስመሰከረች እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማ ጉዞም የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎችን እውን እንዲሆኑ ለማስቻል ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ መነሻነት የተሰሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የጽዱ-ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የከተሞችን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ የዜጎችን ጤናማ የኑሮ ምኅዳር እያጎናጸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤም ኢትዮጵያ በውሃ ደህንነትና ንጽህናቸው የተጠበቁ ከተሞችን ለመገንባት ያስመዘገበችውን ስኬት በተሞክሮነት ለማጋራት እንደሚሰራ አንስተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የዘንድሮው ጉባኤ በውሃ አቅርቦትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረት ማድረጉ የውሃና ሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በማስጠበቅ አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።