39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አዲስ አበባ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ተቋሙ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ የሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የተሳተፉባቸው ስብሰባዎች በመዲናዋ መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
እነዚህ መድረኮች ያለምንም ችግር በስኬት መጠናቀቃቸው የፖሊስን እና የሌሎች የጸጥታ ተቋማትን የዝግጁነት ደረጃ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር መሪዎችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የሚሳተፉባቸውን ታላላቅ ስብሰባዎች የማስተናገድ የዳበረ ተሞክሮ እንዳላት ጠቅሰዋል።
39ኛውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በመዲናችን አዲስ አበባ በስኬት ለማካሄድ ከጉባኤው በፊት መከናወን ያለባቸው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በውጤታማነት መፈጸማቸውን ገልፀዋል።
ለጉባኤው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የበርካታ ሀገራት መሪዎችና እንግዶችን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ፣ የትራፊክና የጸጥታ እንቅስቃሴን ማቀናጀት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሀገሪቱን ገጽታ በሚመጥን መልኩ ለጉባኤው ስኬታማነት የጸጥታና ደህንነት ሥራዎች በተደራጀ አግባብ እንደሚከናወኑም አረጋግጠዋል።
እንግዶች ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡበት ጊዜ ጀምሮ ጉባኤውን አጠናቅቀው ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ተገቢው የእጀባና ሌሎች አገልግሎቶችን የተቀላጠፈና አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ነው ያስታወቁት።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መድረክ ሲሆን፣ የፀጥታው ዘርፍ ዝግጁነት ለጉባኤው ስኬታማነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7-8 ቀን 2018 ዓ.ም “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓትን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የህብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ይካሄዳል።