በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በጥናትና ምርምር ለይቶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ሥራ ውጤታማ እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት በጥናትና ምርምር ለይቶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ሥራ ውጤታማ እየሆነ ነው
ባህር ዳር ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ያለውን የማዕድን ሃብት በጥናትና ምርምር ለይቶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ሥራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ማዕድን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ካላቸው ዘርፎች አንዱ ቢሆንም በነበረው ሂደት ከዘርፉ ይገኝ የነበረው ጠቀሜታ እዚህ ግባ የሚባል አልነበርም።
በመደመር መንግስት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ የሆነው ይህ ዘርፍ አሁን ላይ በተሰጠው ትኩረት ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
በርካታ የማዕድን ሀብቶች ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የአማራ ክልልም ለዘርፉ ዕድገት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ ውጤት እየተገኘ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ የማዕድን ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዝናው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ያለውን ሰፊ የማዕድን ሀብት በጥናትና ምርምር ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ ያለው የልየታና የማልማት ሥራም ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ከወርቅና ኦፓል በተጨማሪ ግራናይት፣ የድንጋይ ከሰል፣ ብረት፣ እምነበረድ፣ ኖራና ሌሎች የማዕድን ሃብቶች በጥራትና በብዛት መኖራቸው በጥናት ተረጋግጧል ነው ያሉት።
በተያዘው በጀት ዓመት ሥድስት ወራት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የተደረጉ 18 የማዕድን ልየታ የጥናት ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን በማንሳት።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በጥናት የተለዩ የማዕድን ሃብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ለ119 ባለሃብቶች የማዕድን ልማት ፍቃድ ተሰጥቷል።
ይህም ሀብቱ እንዲለማና ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በክልሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የማዕድን ሃብቶችን በሀገር ውስጥ መተካትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመከላከልም በየደረጃው ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ።