የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ከ165 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ከ165 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው
ሮቤ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡- ከሕዝቡ ሲነሡ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ከ165 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የባሌ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አብርሃም ኃይሌ አስታወቁ።
ከፕሮጄክቶቹ መካከል 97 ያህሉ አዲስ የተጀመሩ እና ቀሪዎቹ ካለፈው ዓመት የተሻገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እየተገነቡ ካሉት መካከልም የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት፣ መንገድ፣ የጤና ተቋም፤ ትምህርት ቤቶች፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማብለያ፣ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎችን ጨምሮ ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
እስካሁን 40 ፕሮጄክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ ቀሪዎቹን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል።
ለአጠቃላይ ፕሮጄክቶች ግንባታ በሕብረተሰቡ ተሳትፎና በመንግሥት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መመደቡንም አረጋግጠዋል።
የዞኑ የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ኃላፊ ቢኒያም ገብረማርያም፤ የዞኑ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማቸው ከዲዛይን ጀምሮ ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ከተቋራጮች መካከል ኢንጂነር ኢድሪስ አሕመድ በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ የበርበሬ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታን በጥራት በመገንባት በተያዘለት ጊዜ ለማስረከብ ርብርብ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጄክቶች ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውም ነው የተመላከተው።