ቀጥታ፡

በዞኑ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ነጋዴ ባህር፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡-በምእራብ ጎንደር ዞን የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

 በምእራብ ጎንደር ዞን በአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ተካሄዷል። 

የምእራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ፤ የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ የልማት ስራዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጀኔራል ሙላው በየነ፣ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ታጣቂ ኃይሉ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበል በማድረግ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል። 

ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ  በተከናወነ የህግ ማስከበር ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል።

በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

 

ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ ነዋሪ አቶ አበበ ቢሰጥ እንዳሉት፤ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

አካባቢያቸውን ተደራጅተው በመጠበቅ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አቶ እሸቱ መልካሙ ናቸው። 

በመድረኩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የዞንና ወረዳ የስራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም