ከ33 ሺህ የሚልቁ አርሶና አርብቶ አደሮች በእንስሳት መኖ ልማት እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከ33 ሺህ የሚልቁ አርሶና አርብቶ አደሮች በእንስሳት መኖ ልማት እየተሳተፉ ነው
አዳማ፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡- ከ33 ሺህ የሚልቁ አርሶና አርብቶ አደሮች በእንስሳት መኖ ልማት እየተሳተፉ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አብነት ዘገየ ገለጹ።
ከተፈጥሮ ግጦሽ እና ከሰብል ተረፈ ምርት ባሻገር የተሻሻለ መኖን በመስኖ ማልማት የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ አብነት ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በ11 ወረዳዎች የመኖ አቅርቦትን በመጠንና ጥራት ለማሳደግ እየተሠራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
አክለውም 77 ሺህ 561 ሔክታር መሬት ላይ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ማልማት መቻሉን እና በመኖ እየለማ ካላው መሬት 203 ሺህ ቶን ደረቅ መኖ በማምረት አመርቂ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል።
ለተገኘው ስኬትም የአርሶና አርብቶ አደሩ ግንዛቤ ማደግ፣ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥራዎች መጠናከር የሚሉትን በምክንያትነት አንስተዋል።
ለመስኖ የሚውል ውኃ ባለባቸው አካባቢዎች ከሰብልና ከተለያዩ ልማቶች ጋር በማቀናጀት መኖ ማልማት መቻሉም ለውጤቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አመላክተዋል።
የመኖ ልማቱ የግጦሽ እጥረትን ለመቋቋም እና የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ነው ያስገነዘቡት።