የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች መንግሥት እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች መንግሥት እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ ውጤታማ መሆናቸውን ተናገሩ
ሸገር፤ ጥር 20/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት ካደረገልን የመሥሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት በተጨማሪ እየተደረገላቸው ባለው ሙያዊ ድጋፍ ውጤታማ መሆናቸውን የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በፉሪ ክፍለ ከተማ ሙዳ ፉሪ ወረዳ የሚገኘው የባድሪያ፣ ሁሴንና ጓደኞቸቻው ማኅበር አባል ሁሴን አሊዬ፤ ማኅበሩ 2 ሺህ 200 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።
በቀን የሚያገኙትን 180 እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ገቢ እያገኙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም በመንግሥት በተደረገላቸው የመሥሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት ውጤታማ በመሆናቸው የተገኘ ስኬት መሆኑን ጠቁመው፤ ሙያዊ ድጋፍና ክትትልም በየጊዜው እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዚህም ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ከማሥተዳደር ባለፈ ለተለያዩ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በመንግሥት በተመቻቸላቸው ቦታና የብድር አቅርቦት በማኅበር ተደራጅተው 2 ሺህ 500 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማስገባት ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ ሀብታሙ ቀነዓ ናቸው።
አሁን ላይ ለሌሎች ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸው፤ በቀን 2 ሺህ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጫቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የሙዳ ፉሪ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነጌሶ ኬኖ እንዳሉት፤ በወረዳው በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በዚህ ዓመትም ከ450 በላይ ዜጎች በዶሮ ዕርባታ፣ በወተት ልማት፣ በከብት ማድለብና በሌሎች የሥራ መስኮቸ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ከእርሻ ልማት ጎንለጎን በእንስሳት ዕርባታ ኢንሼቲቭ 16 ሺህ ሼዶች በመገንባት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሸገር ከተማ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደጀኔ በቀለ ናቸው።
በተያዘው በጀት ዓመትም የ10 ሺህ 350 ሼዶች ግንባታ መጠናቀቁን ነው ያረጋገጡት።