በክልሉ ከከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል
ሐረር፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል ከከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት እንደሚሰራ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ሰሞኑን ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በወቅቱም ነዋሪዎቹ በተለይም በክልሉ የሚገኙ ባለ ሶስት እግር ታክሲዎች ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና የኮንትራት ስራዎችን ብቻ በመስራት ህዝቡን ለምሬት መዳረጋቸውን አንስተው መንግስት ለዚህ መፍትሄ እንዲሰጥ መጠየቃቸው ይታወሳል።
በዚህም የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ ከሚገኙ ባለ ሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ጋር በዛሬው ዕለት መክረዋል።
የቢሮው ሃላፊ ኢብሳ መሐመድ በወቅቱ እንዳሉት ቢሮው በሐረሪ ክልል ከከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተየያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በአብዛኛው የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎችም የህዝቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ የወጣውን ታሪፍ ለማስተግበር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉና ከተፈቀደው የጭነት ልክ በላይ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል።
ከዚህ አኳያ አገልግሎት ሰጪዎቹ ህግና መመሪያን አክብሮ የመስራትና ህገ- ወጦችን በማጋለጥ ረገድ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸው፤ በተለይም የህዝቡን አገልግሎት በማስቀደም ለከተማዋ አምባሳደሮች መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወንጀልን የሚከላከሉ እንዳሉ ሁሉ ወንጀል ፈጽመው በህግ የተጠየቁ መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ያህያ አብዱሰላም ናቸው።
ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች የኮንትራት አገልግሎት ብቻ በመስጠትና ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ህዝቡን ለምሬት እየዳረጉ መሆኑን ጠቁመው እነዚህ አካላትም በህግ እንደሚጠየቁ አስገንዝበዋል።