ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር ላይ መሳተፋችን ግንኙነታችንን ለማደስ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል - የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር ላይ መሳተፋችን ግንኙነታችንን ለማደስ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ (አፍሪኮም) አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም ገለጹ።

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዛሬው ዕለት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ (ዩኤስ-አፍሪኮም) አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰንን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ግንኙነት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን የጋራ መግለጫም ሰጥተዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በውይይታቸው ሁለቱ ሀገራት የቆየ ግንኙነት ቢኖራቸውም አሁን እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲና ወታደራዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማሳደግ እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በተጨማሪም በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውንና የሁለቱንም ሀገራት ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አሸባሪነትን በጋራ ለመዋጋት መስማማታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ (ዩኤስ-አፍሪኮም) አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አርኤም አንደርሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ታሪክን ለማሰላሰልና የወደፊት ትብብርን ለማጠናከር ትርጉም ያለው አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ምስረታ በዓል አከባበር ላይ ለመገኘትና ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደገና ለማየትም ዕድል እንደሰጣቸው በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

ጉብኝቱ በተለይም የጋራ ቀጣናዊ የደህንነት ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የአጋርነት ዕድሎችን ለመጠቀም እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ አጋጣሚ ስለመፍጠሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም