ቀጥታ፡

በክልሉ ሲካሄድ በቆየው ስፖርታዊ ውድድር አቅም ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች ተለይተዋል

ቦንጋ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲካሄድ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር አቅም ያላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች የተለዩበት መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ለተከታታይ ስድስት ቀናት በቦንጋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ክልል አቀፍ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቋል። 


 

በመድረኩ ማጠቃለያ ለይ የተገኙት የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፣ ስፖርታዊ ውድድሩ ለክልልና ለሀገር የሚበቁ ታዳጊ ስፖርተኞች የተለዩበት እንደሆነ ገልፀዋል።


 

ስፖርት ከውድድርነት አልፎ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃ ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ያነሱት አቶ ፋንታሁን፣ የባህል ስፖርቶችና የባህል ፌስቲቫል በህዝቦች መካከል አንድነትን፣ አብሮነትንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች ክልሉን ወክለው በሀገር ደረጃ ለሚሳተፉ ስፖርተኞች መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ታሪኳ ታከለ በበኩላቸው፣ ስፖርታዊ ውድድሩ የዞኑን እና የከተማውን ያነቃቃ ነበር ብለዋል።


 

ብዙ የባህል ልውውጥ የተካሄደበት፣ አቅምና ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን የተመለከትንበት እና በቀጣይም በዘርፉ መሰራት ያለባቸው ስራዎች የተለዩበት ነበር ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በታዳጊ ወጣቶች ምዘና በእግር ኳስ ስፖርት ዋንጫ ያነሳው የሸካ ዞን የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ዋና አሰልጣኝ ገብርኤል ዜና፣ ታዳጊ ላይ የተጀመረው ስራ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ቀጣይነት ያለው ውድድር ባለመኖሩ በርካታ አቅም ያላቸው ታዳጊዎች ወደ ኋላ ይቀሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ላይ የተጀመረው ስራ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል። 

የሚዛን ስፖርት አካዳሚ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሌ ነገሪ በበኩላቸው፤ በ2016 ዓ.ም ከክልሉ ሁሉም ዞኖች አትሌቶችን በመመልመል ወደስራ በመግባት አሁን 38 ታዳጊዎችን በ8 የስፖርት አይነቶች እያሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል።


 

‎‎አካዳሚው ለዚሁ ውድድር ከ35 በላይ ታዳጊዎችን ማሳተፉን ጠቁመው በውድድሩም የወርቅ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።

‎በመዝጊያው መርሃ ግብር ላይ በባህል ስፖርቶች ውድድር፣ በባህል ፌስቲቫል፣ በታዳጊዎች ምዘና እና በሌሎችም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞችና የባህል ቡድኖች የሜዳሊያ፣ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም