ድርጅቶቹ በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቶቹ በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል
ሀዋሳ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች በሲዳማ ክልል የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚችሉበት የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጋቸውን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሃም ማርሻሎ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል የመንግስትና የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች 5ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል።
የሲዳማ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አብርሃም ማርሻሎ በመድረኩ እንደገለጹት፣ በክልሉ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
መንግስት በራሱ አቅም እንዲሁም ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ተግባራትም ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የበለጠ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።
የክልሉን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጎልበት የድርጅቶቹ ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ተሳትፏቸውን የበለጠ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የሲዳማ ክልል ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ ሃይሉ ሀርሲሳ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማት ተግባራት ላይ ያላቸው ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን ነው የገለጹት።
ድርጅቶቹ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ህዝቡ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተደማሪ አቅም እየፈጠሩ መሆኑንም አንስተዋል።
የሲዳማ ክልል የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝደንት ማስረሻ ክብረት በበኩላቸው፣ በክልሉ የተመዘገቡ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገሪቷ የልማት ተግባራት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የፌዴራል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር መስፍን ሙሉነህ ናቸው።
በኢትዮጵያ ከ7 ሺህ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷቸው በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል::
በሲዳማ ክልል 86 የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች በ161 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ በመሆን የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ።