የጤና ተቋማትን በሕክምና መሳሪያ በማዘመን የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ተቋማትን በሕክምና መሳሪያ በማዘመን የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ የጤና ተቋማትን በሕክምና መሳሪያ በማዘመን የበሽታ መከላከልና አክሞ የማዳን አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የሕክምና አገልግሎቶችን የሚያዘምኑ የላቦራቶሪ ማሽኖችን አበርክቷል።
የተበረከቱት የሕክምና ግብዓቶችም 81’’CBC’’ የተሰኙ የላቦራቶሪ ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች የሕክምና መሳሪያዎችና ሪኤጀንቶች ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ፤ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት የሕክምና አገልግሎቶችን በማሻሻል አመርቂ ውጤት እያስገኙ ነው ብለዋል።
የማርበርግ ቫይረስን በመቆጣጠርና በሽታውን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት የተገኘው ስኬትም ኢትዮጵያ አስተማማኝ የጤና ሥርዓት መገንባቷን እንደሚያሳይም ተናግረዋል።
ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተበረከቱት ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት መስጫ የላብራቶሪ ማሽኖች የጤና ሥርዓቱን በማሻሻል ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጤና ተቋማትን በሕክምና መሳሪያ በማዘመን በእናቶችና ህፃናት ሞትና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ታጋላጭነትን በመከላከል፣ በመቆጣጠርና አክሞ በማዳን በኩል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የጤና ተቋማት ጥራትና ደረጃውን የጠበቁ የሕክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የጤና ተቋማትን ለማዘመን የሚቀርቡ የሕክምና መሳሪያዎች፣ የመድኃኒት እና ሌሎች ግብዓቶች የጤና ተቋማትን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት እያሻሻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተበረከቱት ዘመናዊ የላቦራቶሪ ማሽኖችም የጤና ተቋማትን አገልግሎት በማሻሻል በኩል አይነተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ ዳሊቶ አህመድ፤ የተበረከተላቸው የሕክምና አገልግሎት መስጫ ዘመናዊ ማሽኖች የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተወካይ ዮሴፍ ተፈራ በበኩላቸው፤ ማሽኖቹ የጤና ተቋማትን የሕክምና አገልግሎት የሚያዘምኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተወካይ ዮናስ ከበደ በበኩላቸው፤ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና ማሽኖች የዜጎችን የህክምና አገልግሎት አቅም ማሳደግ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።