የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እየተሰራ ነው
ወልቂጤ ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የጉራጌ እናቶች የምስጋና ቀን ወይም "አንትሮሽት” ክብረ በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ተካሄዷል።
በወቅቱም የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር እንደተናገሩት፤ በክልሉ የመከባበርና የመተሳሰብ እሴቶችን የሚያጎለብቱ ትውፊቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እየተሰራ ነው።
የ''አንትሮሽት'' በዓል በቤተ-ጉራጌ በየዓመቱ ጥር ወር ለእናቶች ክብርና ምስጋና የሚሰጥበት በዓል መሆኑን ጠቁመው ይህም የመከባበር፣ የመተባበር፣ የሰላም እና የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ ማስቻሉን ገልጸዋል።
''አንትሮሽት'' የሴቶች ጥንካሬና ብርታት የሚገለፅበት በዓል መሆኑን ጠቁመው በጥረታቸውም የማህበረሰቡን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ረገድ ለሚጫወቱት ሚና የሚመሰገኑበት ስርዓት መሆኑንም አመልክተዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በበዓሉ እናቶች በቤተሰባቸው፣ በጎረቤቶቻቸው እና በማህበረሰቡ ዘንድ አክብሮትና ምስጋና ይቸራቸዋል ብለዋል።
ዞኑ መሰል ባህላዊ እሴቶች ታሪካዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ነጅምያ መሃሙድ፤ ''አንትሮሽት'' የጉራጌ ሴቶች የመብት ጥያቄ ያነሱበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
መሰል አኩሪ ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለማስተዋወቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።