ቀጥታ፡

ከተማዋ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጋትን መሰረተ ልማት አሟልታለች

ገንዳውኃ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦የምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ  በአምራች ኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጋትን መሰረተ ልማት አሟልታ ባለሀብቶችን እየጠበቀች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። 

የከተማዋን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማስተዋወቅ "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሃመድ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ከተማዋ በአምራች ኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚያደርጋትን መሰረተ ልማት አሟልታለች።


 

ከተማዋ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ይህን ዕድል በመጠቀም መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል።

ከተማዋ የአልጣሽና የጎደቤ ብሔራዊ ፓርኮችን ጨምሮ የበርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሃብቶች መገኛ እንደመሆኗ በቱሪዝም ዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ተመራጭ መዳረሻ ትሆናለች ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሆነ መሰረተ ልማት ማሟላቱንና በቂ የኢንቨስትመንት መሬት ማዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ለአገልግሎት ዘርፍ የሚውልና መሰረተ ልማት የተሟላለት ከ35 ሄክታር በላይ የኢንቨስትመንት ቦታ ማዘጋጀቱም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

የተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ቦታም የመንገድ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች መሰረተ ልማት የተሟላለት መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ አሰፋ በበኩላቸው፣በከተማዋ ቀደም ሲል ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቶ ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ባለሀብቶች ከተማዋ ያላትን እምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩም ጠይቀዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊ ባለሃብቶች መካከል ነጋ ጁሃር፤ በከተማዋ በግብርና፣ በትምህርትና በጥጥ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደመሆኗ በቀጣይም በአምራች ኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ ለባለሃብቶች እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ለሆኑ ባለሃብቶች ዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም