ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በነገሌ አርሲ ተሸነፈ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ነገሌ አርሲ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳዊት ተፈራ በ94ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ29 ነጥብ ደረጃውን ከስድስተኛ ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል።


 

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና 33 ነጥብ ላይ ረግቷል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ17 ነጥብ ከነበረበት 17ኛ ደረጃ ወደ 16ኛ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። ሸገር ከተማ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስምንት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም። 

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም