በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል
ጊምቢ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አካል የሆነው የችግኝ ዝግጅት ስራ በተለያዩ ዞኖች በሰፊው እየተካሄደ ይገኛል።
በምዕራብ ወለጋ ዞንም ከበጋ ወራት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ጎን ለጎን የችግኝ ዝግጅት በሰፊው እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ እንደገለጹት፤ በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ ነው።
እየተዘጋጁ ከሚገኙ ችግኞች መካከል አብዛኛዎቹ ለምግብነት የሚውሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ሲሆኑ ለደን እና ለውበት አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችም እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የአቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሙዝና የአናናስ ችግኞች በስፋት እየተዘጋጁ መሆኑን አንስተው ችግኞቹ የሚተከሉት በ66 ሺህ 827 ሄክታር መሬት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
የችግኝ ዝግጅቱ እየተደረገ ያለው ከ2 ሺህ 900 በላይ በሆኑ የመንግስትና የግል ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መሆኑን ጠቅሰው በችግኝ ዝግጅት ስራው ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዞኑ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለተከላ እየተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል።