ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ለስኬቱ የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ለስኬቱ የበኩላችንን እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ምክክሩ ለዘላቂ ልማትና ለሕዝቦች ትስስር መሠረት የሚጥል ነው።
ሂደቱ የኢትዮጵያውያንን ነባር የመመካከርና የመቻቻል እሴቶች መሠረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማና ለሕዝብ ቅርብ ያደርገዋል ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ሀጂ ሀሰን ቀላ በሰጡት አስተያየት፤ የምክክር ኮሚሽኑ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
ምክክሩ የሕዝብ በመሆኑ እኛም እንደ ሀገር ሽማግሌ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ያሉት ሀጂ ሀሰን በጠረጴዛ ዙሪያ መመካከር ወንድማማችነትን በማጎልበት አንድነትን ለማጠናከር የላቀ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ቦሩ ሮባ በበኩላቸው፤ ከምክክር የተሻለ የችግር መፍቻ አማራጭ እንደሌለ በማንሳት፥ የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ሁሉም ዜጋ ከግብ ማድረስ እንዳለበት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የሕዝቡን ነባር የችግር መፍቻ እሴቶች በመጠቀም ስኬታማ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አቶ ጎሊቻ አሬሮ እንደገለጹት፤ ምክክር በኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ የቆየ የችግር መፍቻ ጥበብ ነው።
በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰከን ብሎ መመካከር ከተቻለ፣ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግና ለትውልዱ መሰረት የሚሆን አሻራ ማኖር ይቻላል ነው ያሉት።
ወይዘሮ ሞሌ ቦሩ፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በምክክር እንዲቀረፉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ሴቶች ያላቸውን ባሕላዊና ማኅበራዊ እሴቶች ተጠቅመው ለተረጋጋች ሀገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ነዋሪዎቹ ሀገራዊ ምክክሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በዘላቂነት ለማስቀጠል ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም ገልጸዋል።