የውኃ ኃብት አስተዳደር አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የውኃ ኃብት አስተዳደር አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ ነው
ነቀምቴ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦የውኃ ሀብት አስተዳደር አቅምን ለማሳደግ የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብት አስተዳደር አቅሟን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው።
ከነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ የውኃ ሀብት አስተዳደርን ለማጠናከር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመትም የውኃ ኃብትን በአግባቡ ማስተዳደር ይቻል ዘንድ የተፋሰስ ምክር ቤት አዋጅ እንዲጸድቅ መደረጉን አስታውሰዋል።
አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የማስፈጸሚያ ደንብ ለማዘጋጀት ክልሎችን ያሳተፈ የግብዓት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አዋጁ የጋራ ጥቅም መስጠት የሚችሉ ግድቦችንና የተፋሰስ መሰረተ ልማቶችን በጋራ ለመገንባት እና ለማስተዳደር እድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።
አዋጁ በተለይም የውኃ አካላትን ዳርቻ እና ግድቦችን በዘላቂነት ለመጠበቅም አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ ሌሎች የውኃ ሀብት አስተዳደር አቅምን የሚያጎለብቱ የህግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ ይደረጋልም ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የውኃ ተቋማት የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን በዘርፉ የሚስተዋሉ የአገልግሎት ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የከተሞች የውኃ አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በከተሞች የውኃ ቦርድን የማቋቋም፣ ህዝቡን የማስተባበር ስራ እና ዘርፉን በሙያተኛ እንዲመራ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በሀገሪቱ በ22 ከተሞች የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ በካይ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ እንዳይገባ እንዲሁም ከንጹህ ውኃ ጋር እንዳይቀላቀል በማድረግ አጣርቶ ለግብርና ስራ ለማዋል ያስችላል ብለዋል።
በሌላ በኩል በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና በኢነርጂ ዘርፍ የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የኦሮሚያ ክልል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ያከናወነው ተግባር አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ረገድ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየትን ለመቅረፍም ደካማ የስራ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋራጮችን ውል የማቋረጥ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የክልል የውኃ እና ኢነርጂ ቢሮዎች የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በነቀምቴ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።