ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ህብረተሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ አስችሏል 

አሶሳ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ህብረተሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ማስቻሉን የኢትዮጵያ የደን ልማት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በርካታ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው እንዲሁም የደን ሽፋንን የሚያሳድጉ ችግኞች እንዲተከሉ አድርጓል።

በተለይም የመሬት መራቆት እና የአየር ንብረት ለውጥ በስነ ምህዳር ላይ አሉታዊ ተዕፅኖ እንዳያመጣ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ለሌሎች ሀገራትም ምሳሌ መሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት በየዓመቱ እስከ 92 ሺህ ሄክታር ደን እንደሚወድም አስታውሰዋል።


 

መንግስት በጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋንን በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2030 ላይ 30 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአሁኑ ሰዓት 23 በመቶ ላይ ያለ መሆኑን ጠቅሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ህብረተሰቡ የደን ምርት አስፈላጊነትን እንዲገነዘብ አድርጓል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ለቀጠናው ሀገራት የውሃ ሀብት እንዲጨምር እና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲስተካከል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የአሁኑ የበጋ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ደኖች አካባቢ የሰደድ እሳት እንዳይነሳ ቀድመው መከላከል እንዲችሉ በሳተላይት የታገዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ህብረተሰቡ ለደን ልማት የሰጠው ትኩረት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው በተሰራው ስራ በየዓመቱ የሚወድመው ደን እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት የሚገኘው የቀርከሃ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል እና የቀርከሃ ችግኞችን በመትከል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የቀርከሃ ደን እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የቀርከሃ ደን ሽፋንን ለማሳደግ በየዓመቱ ከ50 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እየተተከለ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም