የጊፋታን እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማሸጋገር ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጊፋታን እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማሸጋገር ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል "ጊፋታ" ያሉትን እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማሸጋገር እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
የጊፋታ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን አስመልክቶ "የጊፋታ ብስራቶች ለህዝባችን ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጊፋታ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ የወላይታ ህዝብ የአብሮነት መገለጫ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ በዩኔስኮ መመዝገቡ የክልሉን የቱሪስት ፍሰት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ ያሉትን የአብሮነት፣ የይቅርታና የፍቅር እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማሸጋገር በክልሉ መንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከጎላ የባህል እሴቶች መካከል ጊፋታ ተጠቃሽ ነው ያሉት ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው።
የጊፋታ በዓል ተጠብቆ እንዲቆይ ሚኒስቴሩ የበኩሉን እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ጊፋታ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የፈጠረ የህዝባችን ኩራት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሕብረብሔራዊነት የደመቀች ሀገር መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሯ ለጊፋታ በዓል የተሰጠው ትኩረትና ክብር ለዓለም ቅርስነት እንዲበቃ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የአንድነት፣ የመተሳሰብና የፍቅር እሴት ያለው ይህ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ በሀገር ደረጃ በተቋሙ የተመዘገቡ ቅርሶችን ቁጥር ወደ 18 ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት።
መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ለሚሰራው ተግባርም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አክለዋል።
ጊፋታ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ በመቆየቱ በመጣው ውጤት ደስታ ተሰምቶኛል ያሉት ደግሞ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ናቸው።
ይህን በዓል ጠብቀው ያቆዩ አባቶችን አመስግነው የዩኔስኮ አባላት በየጊዜው በመገምገም ቀጣይነቱን ስለሚያረጋግጡ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የወላይታ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ጊፋታ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በህዝብ ዘንድ ታላቅ ደስታ መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።
በዓሉ ህዝቡ ወደ አዲስ ዓመት ያሻገረውን ፈጣሪ የሚያመሰግንበትና ለመጪው አዲስ ዓመት መልካሙን የሚመኝበት መሆኑንም ተናግረዋል።