ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን የማስቀጠል ተግባር በትኩረት ይከናወናል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሀረር፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን የማስቀጠል ተግባር በትኩረት እንደሚከናወን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባዔ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት አካሄዷል።


 

ጉባዔው ባለፉት ስድስት ወራት በቅርስ ጥበቃና የሐረሪ ቋንቋን በማሳደግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን በክልሉ ባህል ቅርስ፣  ቱሪዝምና ትምህርት ቢሮዎች በኩል ቀርበው ገምግሟል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በጉባዔው ላይ እንዳሉት፤ ባለፉት 6 ወራት በክልሉ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በክልሉ በቅርስ ጥበቃና የሐረሪ ቋንቋን በማሳደግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም  የጁገል ቅርስን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ላይ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እና ለዜጎች ተስፋ የሰጡ መሆናቸውንም አክለዋል።

ሆኖም የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች መኖራቸውን በመጠቆም ፅንፈኞችን በመታገል የጀመርናቸውን የልማት ስራዎች አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በዚህም በተጀመሩ የልማት ስራዎች ላይ የአስተሳሰብና የአመለካከት አንድነትን በማጎልበትና ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ረገድ የተሰሩ ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ጉባዔው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም