ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ተጨማሪ ዘጠኝ የ"አዲስ መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ተጨማሪ ዘጠኝ የ"አዲስ መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ ገለጹ፡፡ 

ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡


 

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ55ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

በማዕከሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የሚሰጠው አገልግሎት በተገልጋዮች ዘንድ እርካታን እንደፈጠረ ማመልከቱን ጠቁመው፤ ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር 107 የነበሩት የአገልግሎት ዓይነቶች አሁን ላይ ወደ 132 ማደጋቸውን አስታውቀዋል።

በቅርቡ ተጨማሪ አራት ተቋማት ወደ ማዕከሉ እንደሚገቡ ገልጸው፤ ይህም የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። 


 

የአገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎችም ሥነ-ምግባርን ከቴክኖሎጂ ክህሎት ጋር አጣምረው እንዲሰሩ መደረጉ ለተመዘገበው ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በዋና መሥሪያ ቤትና በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ይህንን ተደራሽነት ለማስፋት ዘጠኝ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም በጉለሌ፣ አዲስ ከተማ፣ ቂርቆስና ልደታ ክፍለ ከተሞች አማካይ ቦታዎች ላይ የሚገኙ አራት ቅርንጫፎች የሕንጻ እድሳታቸው እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅድሚያ ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል፡፡


 

በቀሪዎቹ አምስት ክፍለ ከተሞችም በተመሳሳይ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን መጀመር የሚያስችሉ የግንባታ ሥራዎች እየተፋጠኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከአገልግሎት መስፋፋቱ ጎን ለጎን ማዕከላቱን ለተገልጋዮች ይበልጥ ምቹ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ዮናስ ገልጸዋል። 

ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ሕጻናትን ይዘው ለሚመጡ ተገልጋዮች የሕጻናት ማቆያ ከመገንባት ባለፈ፣ ተገልጋዮች የጤና እርዳታ የሚያገኙበት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም መንጃ ፈቃድ የሚያሳድሱ ተገልጋዮች ለማሽከርከር ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የጤና ምርመራ አገልግሎትን በዚያው በማዕከሉ እንዲያገኙ ለማስቻል ከከተማዋ ጤና ቢሮ ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም