ቀጥታ፡

የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ቅንጅታዊ ሥራው ይጠናከራል

ጂንካ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ገለጸ።

በምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባዔ ዓለማየሁ ባውዲ የተመራ ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ እየተገነባ ያለውን የካራ-ዱስ የፀሐይ ኃይል መስኖ ፕሮጀክት ጎብኝቷል።


 

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጌታነህ ተሾመ ባደረጉት ገለጻ ግንባታው ባሳለፍነው መስከረም ወር መጀመሩን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱን ግንባታ በስምንት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው 40 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሚሊዮን ተክሌ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በ115 ሚሊየን ብር ወጪ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ ከ113 ሔክታር በላይ መሬት ለማልማት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ከመስኖ ፕሮጀክቱ ውኃ ለመሳብ የሚያስችል የፀሐይ ኃይል በአካባቢው እየተገነባ መሆኑም አስረድተዋል።


 

አፈ-ጉባኤ ዓለማየሁ በዚሁ ወቅት የአርብቶ አደሩ የመስኖ ልማት ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካባቢው ያለውን ሀብትና ፀጋ አሟጦ በመጠቀም አርብቶ አደሩን ከተረጂነት ለማላቀቅ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ በቅንጅትና በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።

መንግሥት የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የአካባቢውን አርብቶ አደር ወክለው ንግግር ያደረጉት የካራ-ዱስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዳንኤል ግርጃ ናቸው።

የካራ-ዱስ የፀሐይ ኃይል መስኖ ፕሮጀክት የአካባቢው ነዋሪዎች የብዙ ዓመታት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ እንደነበርም አውስተዋል።

በመሆኑም መንግሥት የአርብቶ አደሩን ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ መስጠቱ የሚያስመሠግን ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም