ቀጥታ፡

ባቱ ከተማን በይበልጥ ለነዋሪዎችና ቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- የባቱ ከተማን የኮሪደር ልማት ከባቱ ሐይቅ ጋር በማሰናሰል ለነዋሪዎችና ቱሪስቶች በይበልጥ ምቹ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ አሕመዲን እስማኤል ተናገሩ።


 

የባቱ ሐይቅን የውኃ ደኅንነት በጠበቀ መልኩ በዳርቻው የመዝናኛና ሌሎችም ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሐይቁን ዕይታ ከከተማዋ ውበት ጋር በማሰናሰል አሁን ላይ 14 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት መከናወኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚሰሩ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።


 

በሐይቁ ዳርቻ የእግረኛ፣ የሳይክልና አስፋልት መንገዶች እንዲሁም የመዝናኛ ስፍራና መናፈሻ ማዕከላት መገንባታቸውንም አብራርተዋል።

ይህም ከተማዋን በይበልጥ ምቹ መኖሪያና የቱሪስት ማዕከል ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል።


 

በሌላ በኩል የአገልገሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ መሶብን ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል አገልግሎቶችን ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል።

በዚህም መሠረት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር የሕንጻ ግንባታ ተጠናቅቆ የቴክኖሎጂ ዝርጋታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም