ቀጥታ፡

ዘመናዊ የሕክምና ግብዓቶች የአገልግሎት ጥራትን እያሻሻሉ ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- ለጤና ተቋማት የሚቀርቡ ዘመናዊ የሕክምና ግብዓቶች የአገልግሎት ጥራትን በተግባር እያሻሻሉ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ ለድሬዳዋ አሥተዳደር እንዲሁም ለተለያዩ ክልሎች ማሽኖችና የሕክምና ግብዓቶችን አስረክቧል።

በዚሁ ወቅት 81 ’’CBC’’ የተሰኙ የላቦራቶሪ ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎች እና ሪኤጀንቶች ርክክብ ተደርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በዚሁ ወቅት፤ የጤና ሥርዓቱን ጠንካራና አስተማማኝ ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ዛሬ ርክክብ የተደረገባቸው ማሽኖችና የሕክምና ግብዓቶችም ለጤና ሥርዓቱ ተጨማሪ ዐቅም መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ ተላላፊ የሆኑና ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ብሎም አክሞ ማዳን የሚያስችሉ ተጨማሪ ግብዓቶች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

የሕክምና ግብዓቶቹ የጤና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና ዘመናዊ የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ከ5 ሺህ በላይ ከሆኑ ተቋማት ጋር ውል ተፈራርሞ የሕክምና ግብዓቶችን በማቅረብ ላይ መሆኑንም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል አገልግሎቱ በቀጣይ ከጤና ተቋማት ጋር ለሚኖረው ተጨማሪ ግብዓቶችን ማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም