ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ ሥራ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ ሥራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፤ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ መርቀው በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከ11 ሺህ 400 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ እና በአገሪቱ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነ የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንፃ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በዚህም ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነትና ብክለትን በማስቀረት፣ የገበያ ማረጋጋትን በመፍጠር እንዲሁም በአምራቹ የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦዎች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለሸማቹ ማህበረሰብ እና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ሸማቹ ማህበረሰብ በተገቢ ዋጋ ትኩስ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ለከተማ አስተዳደሩ ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ይዞታ በማቅረብ ያደረገውን ድጋፍ በሌሎችም ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።
ፕሮጀክቱ ለግብርና ምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ በዘርፉ የአገራችንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተቋማትን አመስግነዋል።