ቀጥታ፡

ቡናን የጎብኚዎች መዳረሻ ለማድረግ የተቀናጁ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ጅማ፣ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- የቡና ልማት፣ የምርት ሂደት እና የአፈላል ሥርዓቱን ከሌሎች የቱሪዝም ሀብቶች ጋር በማስተሣሠር የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጅማ ከተማ የቡና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መስኅብና ምርት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሳ ከድር እንዳሉት፤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከቡና ጋር የማሥተሣሠር ሥራ እየተሠራ ነው።

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር እንደመሆኗ ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች የቡና ምርት ሂደት እንዲሁም የቡናችንን ልዩ ጣዕም እንዲቀምሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የቡና ልማት፣ ምርት ሂደትን እና የአፈላል ሥርዓቱን ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በማሥተሣሠር የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የቡና ምርት ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመረው ሥራ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ላይ ታዋቂነቱን እና ተፈላጊነቱን ለመጨመር ያግዛል ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ክልሉ ቡና በብዛት የሚመረትበት እንደመሆኑ ቡናን ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር ለማሥተሣሠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቡና ከአፈላል ሥርዓቱ ጀምሮ የጎብኚዎችን ትኩረት የሚሰብ በመሆኑ ይህን ዕድል ተጨማሪ የቱሪዝም ሀብት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የቱሪስት መስኅቦችን ለሚጎበኙ የቡና ምርታችንን ጥራት ማሳየት እንዲቻልም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም