የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን የመሪነት ሚና እንዲወጣ አስችሏል- ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን የመሪነት ሚና እንዲወጣ አስችሏል- ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2018 (ኢዜአ)፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን የመሪነት ሚና እንዲወጣ ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር እና የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አሕመድ ሺዴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የእርስዎ እርካታ የባንካችን ስኬት” በሚል መሪ ሐሳብ የደንበኞች አገልግሎት ሣምንት የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር እያካሄደ ነው።
አቶ አሕመድ በዚሁ ወቅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጠንካራ እድገት እያረጋገጠ በስኬት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም የፋይናንስ ዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ውስጥም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ስኬት እየተጓዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መሪ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘርፉ ያለውን የመሪነት ሚና እንዲወጣ ማስቻሉንም አስገንዝበዋል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ45 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናትም አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ እያስገባ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የደንበኞች ሣምንትም ለደንበኞች እና እነርሱን ለሚያገለግሉ ሠራተኞች ያለንን ልዩ ክብር የምንገልጽበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ የባንኩ ስትራቴጂ ዋና አቅጣጫ የደንበኞች እርካታ መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኩ የሚያወጣቸው አሰራሮች እና የሚወስናቸው ውሳኔዎች ደንበኛን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ባንኩ በአጠቃላይ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከደንበኞች ጋር የሚኖር መሥተጋብር ከቴክኖሎጂ እና ከሰው ሀብት ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦፕሬሽን ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍቅረሥላሴ ዘውዱ ናቸው።
ባንኩ በደንበኛ ተኮር ሥራ ቀዳሚ እና ተወዳዳሪ ለመሆን ሰፋፊ ማሻሻያ ማድረጉንም አመላክተዋል።
አክለውም ዓለም አቀፍ የባንክ አሠራር እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሠራተኞች አፈጻጸም መለኪያ መደረጋቸውን አንስተዋል።
የደንበኞች አያያዝ ክኅሎትን ለማስረጽ ተከታታይነት ያላቸው ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ደንበኞች የሚያቀርቡት ቅሬት በአጭር ጊዜ ምላሽ የሚያገኝበት አሠራር መዘርጋቱንም ነው ያመላከቱት።