ቀጥታ፡

በክልሉ የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ዙሪያ የሚዲያ ተቋማቱ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው የሚበረታታ ነው - ቋሚ ኮሚቴው

ባህር ዳር፤ ጥር 2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ዙሪያ የሚዲያ ተቋማቱ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው የሚበረታታ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የአማራ ክልል ቅርንጫፎችን የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርገዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየት የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው አባልና የመስክ ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ አቡኔ ዓለም፤ በአማራ ክልል ቀዳሚው አጀንዳ የዘላቂ ሰላም ግንባታና የልማት ስራዎችን ማከናወን መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት የኢዜአ እና የኢቢሲ የአማራ ክልል ቅርንጫፎች ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን በተለይም በሰላም ግንባታና የልማት ስራዎችን በተመለከተ የተከናወኑ ተግባራትን አጽኖት ሰጥተው መስራታቸውን ገልጸዋል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ፣ የህግ ማስከበር ጥረት፣ የህዝቡን የሰላም ፍላጎትና በተግባር እያሳየ ያለውን ጠንካራ ትብብር በተመለከተ በሚዲያ ተቋማቱ በተከታታይ ይዘት መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

በሀገራዊ ምክክር፣ በህዝብ የውይይት መድረኮች፣ በግብርና ልማት፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ በአረንጓዴ አሻራና የተለያዩ የልማት ኢንሼቲቮች ዙሪያ የተከናወኑት ስራዎችም የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

በክልሉ የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ዙሪያ የሚዲያ ተቋማቱ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይ በሰላም፣ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።

በተለይም በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደትና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ወይዘሮ አቡኔ፤ የምክር ቤቱም ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም