የሴቶችን ሳይንሳዊ የፈጠራና ክህሎት አቅም በማበልጸግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ሳይንሳዊ የፈጠራና ክህሎት አቅም በማበልጸግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ይሰራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ የሴቶችን ሳይንሳዊ የፈጠራ ክህሎት አቅም በማበልጸግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ የስልጠና መድረክ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለተውጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎችና የሳይንስ መምህራን እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው ለሶስተኛ ጊዜ እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር)፤ የሴቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
የሴቶችን ሳይንሳዊ የፈጠራ ክህሎት አቅም በማበልጸግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራትም አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ስልጠናውም ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት የበለጠ ለማበልጸግ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በቀጣይም የሴቶችን ሳይንሳዊ የፈጠራና ክህሎት አቅም በማበልጸግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኪሩቤል መንበሩ በበኩላቸው፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ አንደሚኖረው ገልጸዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ ሴቶችም የሚያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በማበልጸግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አዳነች አለሙ ስልጠናው በቀጣይ በዘርፉ ለሚኖራቸው የፈጠራ ስራ እና እውቀት መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በዘርፉ የሚያገኙት አዲስ እውቀትም ለተማሪዎቻቸው ለማስገንዘብ እድል ይፈጥርልናል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ፋጡማ መሀመድ ናቸው።