ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተከላከለችበት መንገድ ማንኛውንም ስነ ህይወታዊ ስጋት በብቃት መመከት እንደምትችል ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተከላከለችበት መንገድ ማንኛውንም ስነ ህይወታዊ ስጋት በብቃት መመከት እንደምትችል ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተከላከለችበት መንገድ ማንኛውንም ስነ ህይወታዊ ስጋት በብቃት መመከት እንደምትችል ያሳየ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና የሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ጨርሶ ማጥፋት ችላለች።
በዚህም ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በመከላከል በጥቅምት ወር ተከስቶ የነበረውን የማርበርግን ቫይረስ ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የእውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር ተካሂዷል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዥያን ካሴያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ጠንካራ ርምጃ ወስዳለች።
ኢትዮጵያ ንቁ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ያስመዘገበችው ውጤት መሆኑን በማንሳት፣ ጠንካራ የመከላከል አቅሟን የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድም የጠንካራ የአመራር ብቃት ማሳያ መሆኑን አመልክተው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በመጠቀም ትክክለኛና ዘመኑን የዋጀ ተግባር ማከናወኗን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተገኘው ስኬት ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከላከል ግብረ ሀይል ጋር በትብብር ሲሰራ እንደነበርም ተናግረዋል።
በዚህም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማንሳት፤ ለኢትዮጵያ የበሽታ መከላከል ስርዓት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ነፃ የሆነችበት መንገድ የመንግስትና የማህበረሰቡ ትብብር ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በሽታው በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት በኢትዮጵያ ባለው ግልፅና የተቀናጀ የበሽታ መከላከል ስርዓት ቫይረሱን ማጥፋት ተችሏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በመንግሥት በጤና ተቋማትና በማህበረሰቡ መካከል የነበረው የትብብር እርምጃ በተግባር ለውጥ ማምጣቱን አይተንበታል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ ወቅቱን የጠበቀ ብሔራዊ ትብብር የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ የማርበርግ ቫይረስን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ዘርፎች በጋራ ሲሰሩ እንደነበር በማስታወስ፤ ትብብራቸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል ያደረገችውን ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
እንግሊዝ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም በሽታ ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ታድርጋለች ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር ጠንካራ ምላሽ መስጠቷን ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ ተምረናል ያሉት አምባሳደር ሴም፤ የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል፡፡