ቀጥታ፡

የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ጂንካ፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፡- የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አለማየሁ ባውዲ የተመራ ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደር አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ዛሬ ተመልክቷል።


 

ቡድኑ በዞኑ በናፀማይ ወረዳ በክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የተገነቡ የእንስሳት ግብይትና የኤክስፖርት እንስሳት ማሰባሰቢያ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ተመልክቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።


 

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተገነቡ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላት ህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን በመከላከል ህጋዊ ንግድን ስለሚያጠናክር አርብቶ አደሩ እንስሳቱን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

አርብቶ አደሩን በማህበር በማደራጀት በከብት ማድለብ፣ በእርሻ ሥራና በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች በማሳተፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው መንግስት የክልሉን አርብቶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማሳደግና የድርቅ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በበና ፀማይ ወረዳ የተከናወኑ የእንስሳት ግብይት ማዕከል፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እና ትምህርት ቤቶችን በአብነት  ጠቁመዋል።

የበና-ፀማይ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ በበኩላቸው የተከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች የረጅም ዓመታት የአርብቶ አደሩ የልማት ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በወረዳው አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

ቡድኑ በነገው እለትም በሐመር፣ በኛንጋቶም እና በዳሰነች ወረዳዎች ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችንም እንደሚመለከት ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም