በክልሉ ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች ለአርሶአደሩ ተደራሽ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች ለአርሶአደሩ ተደራሽ እየተደረጉ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 18/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ የግብርና ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች ለአርሶአደሩ ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በባህር ዳር እየተካሄደ ይገኛል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አጀበ ስንሻው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ማሳደግ የሚያስችሉ የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጠ የግብርና ግብዓቶችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአርሶአደሩ እየቀረቡ ነው።
አርሶአደሩ ጥራታቸው የተረጋገጠ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኝ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የግብርና ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂን ተደራሽ ማድረግ ምርታማነትን በዘላቂነት ከማሳደግ ባለፈ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የክልሉ የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባስልጣን ዋና ዳይሬክተር ፈንታሁን ስጦታው በበኩላቸው፤ የግብርና ምርቶች ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል አየተደረገ ነው ብለዋል።
ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ከምርት ሂደት ጀምሮ በማጓጓዝና በክምችት ወቅት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የጥራት ጉድለት ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በዘርፉ የተጀመሩ ተግባራት አበረታች እንደሆኑ አንስተው፤ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሃብታሙ (ዶ/ር) ባለስልጣኑ ለሀገር ወስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2017 እና 2018 በጀት ዓመት በአማራ ክልል ብቻ ቦለቄ፣ ሰሊጥና ሌሎች ምርቶችን ወደ ወጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ከአንድ ሺ በላይ ድርጅቶች የምርት ጥራት ማረጋገጫ መሰጠቱን አመልክተዋል።
የጥራት ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች መጠናከርም የዘርፉን ዘላቂ እድገት ከማረጋገጥ ባሻገር በሰው፣ በእንስሳትና በእፅዋት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመከላከል እንደሚያስችል በማንሳት።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ በየደረጀው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።