በወረዳው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወረዳው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው
አምቦ፤ ጥር 18/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ሲከናወን የቆየው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ በግብርና ዘርፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱ ተገለጸ፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው በዞኑ የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በርካታ ጥቅም እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቀናጀ የአፈርና የውሀ ጥበቃ ስራው ቀደም ሲል በጎርፍ የሚጠረገውን ለም አፈር በማስቀረት ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው የዋጅራ ቀበሌ ነዋሪው ባይሳ ሚደቅሳ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር የሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የግብርና ልማት ስራዎቹን ውጤታማ አድርጓል።
ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት ስራ በጎርፍ ተጠርጎ ተራቁቶ የነበረው መሬት ማገገም በመቻሉ ከአንድ ሄክታር መሬት አራት ኩንታል ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በቶኬ ኩታዬ ወረዳ የማሩፍ ቀበሌ አርሶ አደር አቦምሳ ፊጣ፤ በአካባቢያቸው በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ደርቀው የነበሩ ምንጮች ጭምር መመለስ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የተፋሰስ ልማት የተከናወነበት መሬት በማገገሙ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቀው ከማምረት ወጥተው በአመት ሁለቴ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ተፋሰስ ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች ከሰብል ምርት ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ ለእንስሳት መኖ ልማትም እየጠቀማቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ከግብርና ባለሙያዎች ስልጠና መውሰዳቸውን የጠቀሱት ደግሞ በወረዳው የዋጅራ ቀበሌ አርሶ አደር ጋዲሳ ደንደና ናቸው፡፡
የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ ወይዘሮ ባዳዲ ዱጋሳ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በወረዳው በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የገጸ ምድርና የከርስ ምድር ውሃ በመጎልበቱ የአርሶአደሩ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል፡፡
ስራውን በዘንድሮው ዓመትም በማስቀጠል ከ23 ሺህ በላይ ሰዎችን ክፍሎችን በማሳተፍ 2 ሺህ 234 ሄክታር መሬት የማልማት ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል ፡፡
የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲሳ ሀይሉ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ 273 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በሁሉም ወረዳዎች መጀመሩን ገልጸዋል ።
ባለፈው ዓመታት በዞኑ በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችም የአፈር ለምነትን መጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡